በኢትዮጵያ ያለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ወይስ የጋዜጠኝነት ጣረ ሞት?

በዚህ ጽሁፍ የማቀርብላችሁ ርእሰ ነገር ልማታዊ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ የሚል ነው:: አዲስ ጉዳይ መጽሄት ሰሞኑን በተከታታይ እትሞቿ ስለ ልማታዊ ጋዜጠኝነት የተላያዩ ሰዎችን ሙግት ይዛ ቀርባ ነበር:: መጽሄቷ አንጋፋ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑትን አቶ ማእረጉ በዛባህን ቃለ መጠይቅ በማድረግ እና በመቀጠልም የኝህኑ መምህር ጽሁፍ አንዳንድ ነጥቦች ስለ ልማታዊ ጋዜጠኝነት በሚል ርእስ ለአንባቢ አቅርባለች:: ከቃለ መጠይቁም ሆነ ከቀረበው ጽሁፍ በመነሳት በሀገራችን ልማታዊ ጋዜጠኝነት የሚባለው የጋዜጠኝነት ዘውግ እየተተገበረ ነው ማልት ያዳግታል የሚል ድምዳሚ ላይ እንደርሳለን:: በእውነቱ ከሆነ የአቶ ማእረጉ አቋም የኔም አቋም ነው:: ነገር ግን በዚህ በሳቸው ጽሁፍ አነሳሽነት ሁለት ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር ዝምድና ያላቸው ወጣቶች የለም የአቶ ማእረጉ ድምዳሜ ስህተት ነው ይሉናል :: እንዳውም አቶ ማእረጉ ሆነ ብለው እውነታን ለመካድ በመሻት ልማታዊ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ የለም የሚል የተሳሰተ ድምዳሚ ላይ ካልደረሱ በቀር ኢትዮጵያ ውስጥ ሊካድ በማይቻል ሁኔታ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ውስን ዘውጎች በመንግስት መገናኛ ብዙሀን እና በአንድ አንድ FM ራዲዮን ጣቢያዎች እየተተገበሩ ናቸው ሲሉ የክርክር ነጥባቸውን አቅርበዋል:: ይህ የነዚህ ሁለት ወጣቶች አቋም የነሱ ብቻ አቋም አድርጌ አልመለከተውም:: የመንግስትም አቋም እንደሆነ አምናለሁ:: አለመታደል ሆኖ እንጂ መንግስት ለዲሞክራሲ መጎልበት እንዲህ መሰረታዊ ፋይዳቸው ላቅ ያሉ ጉዳዮችን አደባባይ አውጥቶ ሕዝባዊና ምሁራዊ ክርክሮች እንዲካሄዱ ከመፍቀድም አልፎ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበረበት ግን አልሆነለትም፤ ወደ ምክንያቶቹ አልሄድም የጽሁፌ ትኩረት አይደለምና። የግል መገናኛ ብዙሃንም ቢሆኑ ጥቂቱ በሀገር ውስጥ ግማሹ ከሀገር ውጪ በመሆን እንዲህ ያለውን ጉዳይ በተንጠባጠበ እና አልፎ አልፎ በሚነሳ የአምድ ማሟያነት ከክርክር ባለፈ ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመር የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም በሰፊው ለመስራት በሞከሩ ነበር: ምንም እንኳ የእስካሁኑ ሙከራቸው ቢያስመሰግናቸውም: :

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው/አይደለም የሚለው ክርክር በልማታዊ ጋዜጠኝነት ሀልዮቶች ላይ የተንጠለጠለ መሆን የለበትም:: በእርግጥ የ”ልማታዊ” ጋዜጠኝነት ሀልዮቶችን ፋይዳ እና መገለጫዎቹን የ”ልማታዊ” ጋዜጠኞችን ስነ ምግባር እና ሌሎችንም ከርእሰ ጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በሙሉ መነጋገርም መወያየትም ተገቢ ነው:: ነገር ግን ይህን የመሰለ ሀገራዊ አብይ ጉዳይ በሃልዮት ደረጃ ብቻ ተወያይቶ ወይም “ምናምን” ብሮድካስት ኮርፖሬሽን፤ በሚባለው ራድዮ ጣቢያ አንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ ምንትስ ስለሚባል ሰፈር ወጣቶች ድህነትትን ለመዋጋት በማሀበር ስለመደራጀታቸው ሰምቻለሁ::ምንትስ በሚባለው FM ራድዮ ዜጎች ያለ ፍራሃት በስነተዋልዶ ጤና ሲወያዩ ሰምቻለሁ :አይቻለሁ :: ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው ብሎ አፍን ሞልቶ ማውራት ይችላል ለሚሉ ባልዳረባዎቼ : እኔ ልላቸው የምቸለው ነገር ቢኖር እነዚህ የክርክር ነጥቦች የየዋህነት ካላያም የጅለነት ወይም ድግሞ አውቆ የተኛ አይነት የመካራከሪያ ነጥቦች ናቸው:: ምክኒያቱም ልማታዊ ጋዜጠኝነት በሃልዮት ደረጃ እንኳ በቅጡ ያልተደላደለ ወጥ የሆነ የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር የሌለው ከምእራባዊያን የጋዜጠኝነት ባህል እንኳ በምን እንደሚለይ ጥርት ባለ ሁናቴ ሳይታወቅ: በኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው ብሎ በችኮላ ከመደንገግ በፊት: የሀገራችንን የሚዲያ መልእካ፡ምድር(Media Landscape)፣ ህጋዊ ዳራቸውን እና ጋዜጠኞቻችን ሙያቸውን እየተገበሩ ያሉበትን አውድ በሚገባ ዘርዘር አድርጎ ማየቱ ይቀድማል ብዬ ሰለማምን ነው::ከዚህም ባሻገር የመገናኛ ብዙሃን የስራ ባህል እና የጋዜጠኝነት ልምድ ትንተና ባንድ አገር ውስጥ ካላቸው ተጨባጭ ኹኔታ ነው መጀመር ያለበት። እስቲ ተጨባጩን የአገራችንን የመገናኛ ብዙሃን የስራ ባህል እና የጋዜጠኝነትን ስራ አንኳር ነጥቦች በወፍ በረር እንቃኛቸው፦

በሀገራችን የሚዲያ መልእካ፡ምድር ላይ የሚገኙትን እድሜ ጠገብ እና ሰፊ ጂኦግራፊያዊ ተደራሽነት ያላቸውን የመገናኛ ብዙሃን ፦ኢቴቪ፡የኢትዮጵያ ራዲዮ እና አዲስ ዘመንን ጨምሮ በየክልሉ የሚገኙትን የመገናኛ ብዙሃንን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው መንግስት ነው:: ይህም በአዋጅ የተረጋገጠለት መብቱ ነው:: ነገር ግን መንግስትም ይሁን ግለሰብ በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የትኛውም የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ትርፍን ከማጋበሻነት በተጨማሪ የባለንብረቱን የፖለቲካ አቋም ማራመጃ ለመሆን ምቹ ነው:: በዚህ ጉዳይ ላይ የመገናኛ ብዙሃንን የፖለቲካ፡ኢኮኖሚ(Poletical Economy of the Mass Media) በመተንተን እውቅ የሆኑት ኖኦም ቾምስኪን እና ኤድዋርድ ሄርማን በ 1988 “ይሁንታን ማመረት”(Manufacturing Consent: The Political Economy of the Mass Media) በሚል ርእስ ካሳተሙት መጻህፍ የፕሮፓጋንዳ ሞዴል የሚለው ጽንሰ ሀሳብ የሀገራችንን የመገናኛ ብዙሃን መልእካ፡ምድር እና የፖለቲካ፡ኢኮኖሚ በደንብ አድምቶ ስለሚገልጽልኝ ዋቤ ዕድርጌ ከዚህ እንደሚከተለው እጠቀስዋለሁ(ትርጉም ራሴ)፦

መሰረታዊ የሀብት እና የፖለቲካ ስልጣን ክፍፍል መዛነፍ በሰፊው በሚስተዋልባቸው ሀገራት መገናኛ ብዙሃን ስልታዊ በሆነ ዘዴ የሚስተዋለውን እለመመጣጠን የማድበስበስ ታላቅ ሚናን ይጫወታሉ:: በተለይም የስልጣን መዘውሩን የሚቆጣጠሩት ጥቂት ቢሮከራቶች ከሆኑ እና ሞኖፖላዊ የመገናኛ ብዙሃን ቁጥጥር የሰፈነበት ስራዕት ከሆነ በተለይ ደግሞ ህጋዊም ሆነ ህገ ወጥ (ጭማሪ ከራሴ) የቅድመ ምርመራ አሰራርን የሚያበረታታ ከሆነ የመገናኛ ብዙሃን ስልጣን ላይ ለሚገኙት ልሂቃን ጥቅማቸውን ማስጠበቂያ መሳሪያ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው:: (ገጽ 1 1988)

ይህ ማለት ደግሞ መንግስታት የህዝቡን አስተያየት በመገናኛ ብዙሃን በኩል በሚገባ ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው እድል ይፈጥርላቸዋል ማለት ነው:: በዚህም መሰረት መንግስታት በቁጥጥራቸው ስር የሚገኙትን መገናኛ ብዙሃን በመጠቀም ህዝቡ ወይም ጋዜጠኛው በራሱ ተነሳሽነት የመረጠውን ርዕሰ ጉዳይ ወይም በወቅቱ እየሆነ ያለውን እንገግጋቢ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ወደ ጎን በመተው የራሳቸውን እጀንዳ ማራጋቢያ እና የኢኮኖሚ ጥቅም ማስጠበቂያ ያረጉታል ማለት ነው::

ለጥቄ ይህንን በምሳሌ ላስረዳ ተከተሉኝ ::በሀገራችን የሚዲያ መልእካምድር ላይ ከላይ ከጠቀስኩት የቾምስኪ እና የሄርማን ሀልዮት አንጻር በግሉም ሆነ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን የሚስተዋሉ የባለቤትነት ቁጥጥር ምሳሌዎችን በደምሳሳው ልጠቃቀስ:: ላካሄድ እንዲያመቸን ከስርጭት ሽፋን ተደራሽነት እና ስለ መንግስት መገናኛ ብዙሃን በአይነ ህሊናችን ስናስብ ሁልዜም ድቅን ስለሚልበን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ፊት እውራሪ ከሆነው ኢቴቪ ልጀምር:: መንግስት ኢቴቪን ልክ እንደ ሀረር ሰንጋ ገመድ በእንገቱ ላይ አስሮ ወደ ፈለገበት እንደሚነዳው ከሚያሳብቅበት የመገናኛ ብዙሃን ቀዳሚው ነው:: በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ላይ የፍልስፍና ዲግሪ ጽሁፋቸውን የጻፉት ኖርዊያዊው ቴርዬ ስካርድል (Terje S. Skjerdal) በ 2008 “Conflicting professional obligations among government journalists in Ethiopia” በሚል ርእስ ካሳታሙት የጆርናል ጽሁፍ በመጥቀስ የክርክር ነጥቤን ላጠናክር ለነገሩ የኢቴቪን የመንግስት አፍነት ለማስረዳት ምስክር መጥቀስ አያሻውም:: ከወቀሳ ለመዳን ግን (Terje) ቴርዬ የጆርናል ጽሁፍን ሲጽፍ በማስረጃነት የተጠቀመውን ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የኢቴቪ የእንግሊዝኛ ዴስክ ከፍተኛ ረፖርተር በህዳር 2000 ዓም የኢትዮጵያ የፕሬስ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ስለነበረው የፕሬስ አዋጅ የተቃውሚ ድምጾችን ያካተተ የዜና ዘገባ በመስራቱ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚንስቴር ከነበሩት ከአቶ በረከት ሰሞኦን የደረሰበትን ጫና እንዲህ ያስረዳል (ትርጉም ከራሴ)፦

“የፕሬስ አዋጁ በጣም አፋኝ ነው የሚል እስተያየት የሚሰጡ ብርካታ ሰዎች እራሱ አቶ በረከት ሰሞኦን በሚመራው በፕሬስ አዋጁ ዙሪያ በተዘጋጀ የውይይት መድረከ ላይ በሰፊው ይደመጡ ነበር:: በመሆኑም በማታው የዜና እወጃ ሰአት በዚህ ዙሪያ ባዘጋጀሁት የዜና ዘገባ ላይ የነዚህን ሰዎች እስተያየት አካትቼ አቀረብኩ::”

“በማግስቱ ግን እዛው ኢቴቪ ህንጻ ላይ ይገኝ ከነበረው ሚንስትር መስሪያ ቤቱ ስልክ ተደውሎ ተጠራሁ:: ሚንስትሩ በሰራሁት የዜና ዘገባ ተበሳጩብኝ:: ለምንስ እንዲህ እይነት ዜና እንደሰራሁ ጠየቁኝ:: እኔም ዜናው ባላንስ እንዲኖረው ወይም ሚዛናዊ እንዲሆን ነው ስል ያለ ምንም ፍርህት ላስረዳችው ሞከርኩ:: እሳቸው ግን ይህ የባላንስ ወይም የሚዛናዊነት ጉዳይ አይደለም:: ይህ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደ መሆኑ መጠን መስበክ ያለብህ ሰለመንግስት ነው:: አሉኝ”::(ገጽ 6 2008)

ሌላ ምሳሌ ልጨምር:: መሀመድ ሰልማን በ2011 ፒያሳ መሃሙድ ጋር ጠብቂኝ በሚል ርእስ ካሳተመው የወጎች እና የመጣጥፎች መድብል መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ላይ ያለውን ቁጥጥር እና የቾምስኪን እና የሄርማንን ሀልዮት ሰነ ጽሁፋዊ ለዛ ባለው መንገድ ሰለሚያስረዳልኝ ኢቴቪ እና ተዛማጅ ትዝታዎቼ ከሚለው መጣጥፍ የኢቴቪ የዜና ቀመር የሚለውን ቃል በቃል እንደሚከተው ገልብጨዋለሁ::

ኢቴቪ አንድን ዜና ዘለግ ላለ ጊዜ እያቦካ የመጠቀም ባህል አለው:: ለምሳሌ ከአላማጣ ማይጨው መንገድ ሊሰራ ነው ብለን ብናስብ ከሚሰራው መንገድ ይልቅ ዜናው እንደሚረዝም በዚህ መልክ ማየት እንችላለን:: በትንሹ ከአንድ መንገድ አስር ዜናዎች ይፈለፈላሉ

1.ከአላማጣ ማይጨው የሚደርሰውን የጠጠር መንገድ ወደ አሥፋልት ለማሳደግ የሚያስችል ብድር ከቻይናው ማክሲም ባንክ ተገኘ።
2.ከአላማጣ ማይጨው የሚደርሰውን የሚገኘውን መንገድ ለመስራት ከቻይናው ሲራቢሲ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተካሔደ::
3.ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደውን መንገድ ለመጀመር የመሰረት ድንጋይ ተጣለ::
4.ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ ተጀመረ::
5.ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው ተባለ::
6.ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ በመጓተቱ ነዋሪዎች ተቸገርን አሉ::
7.ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ 65 በመቶው ተጠናቀቀ::
8.ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃል ተባለ:
9.ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ::
10.ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ በመጠናቀቁ: የአካባቢው ነዋሪዎች ደስታቸውን ገለጹ::

ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ዜና በ10 ተመንዝሮ ሲቀርብለት 10 ጎዳናዎች የተሰሩለት ስለሚመስለው “ይህ መንግስት ምነኛ ልማታዊ ነው” ሲል ይገረማል::”(ገጽ 73/74 2004) ይህዝብ ይሁንታን ማምረት ይሉሃል ይህ ነው:: ውዱ ባልደራባዬ መሀመድ ሆይ የኖኦም ቾምስኪን እና ኤድዋርድ ሄርማን የፕሮፖጋንዳ ሞዴል ኢትዮጵያዊ በሆነ ትንትና ለማስረዳት ስራዪን ምነኛ አቀለልክልኝ::

ከዚህ ባሻገር የመንግስት ጠንካራ የባለቤትነት ቁጥጥር በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተዋልበት ከቅርብ ግዜ ወዲህ እንደ የአዲሱ ዘመን የመገናኛ ብዙሃን አውታር የሚቆጠረው የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ነው:: ከቴሌኮም አገልግሎቶች መሃከል የሞባይል ስልክ አገልግሎት እና ሌሎችም የመረጃ መረብ ወይም የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ከ85 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በብችኝነት የሚያቀርበው ዕትራፊው እና ብቸኛው የኢትዮጵያ ቴሌኮም ኮርፖሬሽን ነው:: ስለ ቴሌኮም የአገልግሎቶት ጥራት መጓደል ተጠቃሚው በሚገባ ስለሚያውቀው በዚህ ጽሁፍ ምንም አልልም:: በዚህ ላይ ተጠቃሚው ለቴሌኮም አገልግሎቶች የሚከፍለው ዋጋ እጅግ ውድ መሆኑን የ2011 የFreedom House ን ሪፖርት ጠቅሶ ነብዩ እያሱ ስደት በጋዜጠኛው አይን በሚለው አዲስ መጻሃፉ ላይ ዘግቧል:: (ገጽ 312 2004):: በአንጻሩ ግን ልማታዊ ጋዜጠኝነት በሰፊው ይተገበርባቸዋል በሚባሉት እንደ ህንድ ባሉ ሀገራት የቴሌኮም አገልግሎቶች የዜጎችን አሳታፊነት በማሳለጥ ዜጎች ለልማት ብቻም ሳይሆን ለመልካም አስተዳደር እና ለግልጽነት መጠናከር የድሮዎቹ የመገናኛ ብዙሃን ተብለው ከሚጠሩት እንደ ሬዴዮ እና ቴሌቭዝን ሁሉ ህብረተሰብን በመቅርጽ ለሀገር እድገት የማይተካ ሚና ይጫወታሉ: :

ከላይ የተቀሱት ማሳያዎች በኢትዮጵያ ሚዲያ መልእካ፡ምድር ላይ አድራጊ ፈጣሪ መንግስት መሆኑን ያረጋግጥልናል:: እላይ በጠቀስኩት የቾምስኪ እና የሄርማን ሀልዮት መሰረት ደግሞ መንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር በሚያሳድርባችው ሀገራት መገናኛ ብዙሃን የህዝብን ይሁንታ በማመረት ስራ ነው የሚጠመዱት:: ይህንንም ስራቸውን(ይሁንታ ማመረትን) የዳቦ ስም አውጠተውለት ልማታዊ ጋዜጠኝነት ይሉታል እንጂ ልማታዊ ጋዜጠኝነት የሚባል ነገር የለም: ለኔ ባሀገራችን የሚዲያ መልእካ፡ምድር ላይ ዛሬ የሚሥተዋለው ከዚህ ብዙም የሚለይ አይደለም:: አቶ ማእረጉም ለማለት የፈለጉት ይህንኑ ይመስለኛል::እስቲ አሁን ደግሞ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ህግ ምን ይላል::

ልማታዊ ጋዜጠኝነት ከህግ አንጻር ያስኬዳል?

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29 ዜጎች ዘርፈ ብዙ ከሆኑ የመገናኛ ብዙሀን መረጃን የማግኝት እና የመሰላቸውን አስተያየት የመያዝ መብታቸው ተረጋግጦላቸዋል:: በተለይ ደግም በአንቀጽ 29 ንኡስ አንቀጽ 5 መሰረት በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሀንም እንኳ ቢሆኑ የአስተሳሰብ እና የአስተያየት ብዙሃነትን (Diversity of Expression and Opinion) ማረጋገጥ አለባቸው:: በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ የተደረጉበት ምክኒያት ይህንኑ ለማድረግ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሀን እና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 መገናኛ ብዙሀን በነጻነት ስራቸውን ማከናወን እንዲችሉ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በድጋሜ አረጋግጧል:: እዚህ ላይ እንዲተኮርበት የምፈልገው ነጥብ ታዲያ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚተዳደሩ የመገናኛ ብዙሀን እና የነዚሁ ድርጅቶች ምንደኛ ጋዜጠኞች የአስተሳሰብ እና የአስተያየት ብዙሃነትን በተግባር ለማረጋገጥ መትጋት አለባቸው እንጂ በልማታዊ ጋዜጠኝነት ስም እራሳቸውን እንደ ሀገር ገንቢዎችም ሆነ እንደ መንግስት አጋሮች በመቁጠር ህገ መንግስቱ በአንቀጽ 29 ንኡስ አንቀጽ 5 ያረጋገጠውን ዲሞክራሲያዊ መብት እንዲጣስ ተባባሪ መሆን የለባቸውም:: ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ትልልቅ መንግስታዊ አጀንዳዎችን ለሀገሪቱ ብቸኛ ና መለኮታዊ መፍትሄ አድርገው ያቀርባሉ መንግስትን የሚተቹ ዜጎችን ደግሞ ትችቱ ለምን እንኳ እንደተሰነዘረ ቀርበው እንዲያስረዱ ሳያደርጉ የሀገር ጠላቶች እና መርዶ ነጋሪ እንደሆኑ ተደርገው ይቀርባሉ:: ከህጉ አንጻር ግን ይህ የመብት ጥሰት እንጂ ልማታዊ ጋዜጠኝነት አይደለም:: ለኔ አንድ ጋዜጠኛ በከፍተኛ የሞያ ልቀት እና የሰነ ምግባር ብቃት ያለ መንግስትም ሆነ ያለ ቱጃር ተጽእኖ በነጻነት ስራውን ከሰራ እሱ ጋዜጠኛ ነው:: ከፈለጋችሁ ልማታዊ የሚል ቅጥያ ልትጨምሩበት ትችላላሁ::

ነጻ የግል መገናኛ ብዙሃንስ?

በግል የመገናኛ ብዙሃንም ቢሆን የተጋነኑ “ልማታዊ” ዜናዎች ባይስተዋልባቸውም:: በማስታወቂያ አስነጋሪዎች ተጽእኖ ምክኒያት ማስታወቂያዊ ዜናዎችን :ማስታወቂያዊ ዶክመንተሪዎችን እና ሌሎችንም ፕርግራሞች (Adevertorials) ማየትም መስማትም እየተለመደ መጥቷል:: በኤፍ ኤሞቻችንም ሆነ በጋዜጦቻችን አንዳንድ ዘገባዎች ላይ እነዚህን ክፉ የጋዜጠኝነት ተግዳሮቶች አልፎ አልፎ አያለሁ:: ስም ሳልጠቅስ ምሳሌ ልስጥ: አንድ ማንትስ የሚባል ወፍ ዘራሽ ቱጃር BIKS የሚባል ብስኩት ፋብሪካ በቅርቡ ከፍቷል ወይም አለው እንበል:: ይህ ወፍ ዘራሽ ቱጃር ብስኩቱን በገፍ መሸጥ ይፈልግ ስለነበር ማስታወቂያ ማሰራት ያስባል:: ከተማው ውስጥ ያሉት የማስታወቂያ ለፋፊ ድርጅቶች በደቂቃ ታይታ/ተሰምታ ለምታበቃ ማስታወቂያ ዋጋቸው የሚቀመስ አለሆለትም:: በዚህ ላይ ማስታወቂያ ማስታወቂያ ነው:: በአጋጣሚ አንድ ቀን ይህ ባለሀብት ማንትስ ልማት ማህበር ባዘጋጅው ቴሌቶን ላይ አንድ ሁልግዜ በራዲዮ ድምጹን እየሰማ ባካል ግን የማያውቀውን ትንታግ ልማታዊ ጋዜጠኛ ይተዋወቃል:: አጋጣሚውንም በመጠቀም ለልማታዊ ጋዜጠኛው ማስታወቂያ ማሰራት ፈልጎ ዋጋው አልቀመስ እንዳለው ይነግረዋል መፍትሄ ካለውም እንዲያማክረውም ይጠይቀዋል:: ጋዜጠኛውም የሆነ አካባቢ ስለሚኖሩ ምንዱባን ያአኗኗር ችግር የሚመለክት የራዲዮ ዶክመንተሪ ለመስራት እያሰብኩ ነው ይህንን ፐሮግራም በአነስተኛ ዋጋ ስፖንሰር አድርግና ስለ BIKS ብስኩት ፋብሪካ ሰፋ ያለ እና ተከታታይ የዜና ዘገባ ላቅርብልህ የሚል የልማታዊ ጋዜጠኝነት ሞያዊ ምክሩን ሰጠው:: በዚህም ተስማሙ ባለጸጋውም ከፍተኛ ከሆነ የማስታወቂያ ወጪ ከመዳኑም ባሻገር በቀላል ወጪ የኩባንያውን ስም በተጋጋሚ ማህበራዊ ችግሮችን ከሚፍቱ ልማታዊ ሀገር በቀል ኩባንያዎች ተርታ ተሰለፈለት:: ህዝቡም ይህንን ልማታዊ ባለጸጋ ላሀገር አሳቢ ለደሀ አዛኝ አድርጎ ስለሚያስበው ብስኩት ሲገዛ ሁልግዜም የ BIKSን ነው::

እዚህ ላይ ግን የማስታወቂያ አስነጋሪ ባለሀብቶች የዜና ሽፋን ስጠኝ እና ማስታወቂያ ልስጥህ ተጸእኖ የትም ሀገር ላይ ያለ ተጸእኖ ስለመሆኑ ዋቤ መጥቀስ አያሻውም ቢሆንም ግን እንደኛ የፋይናንስ ነጻነታቸው እጀግ ፈታኝ እና እስቸጋሪ የሚሆኑባቸው የግል መገናኛ ብዙሀን በሚገኙባቸው ሀገራት ማስታወቂያዊ ዜናዎችን በልማታዊ ጋዜጠኝነት ስም መስራት መፍትሄ የሌለው መሆኑን እገነዘባለሁ:: የሀገራችን በተለይ የህትመት የግል መገናኛ ብዙሃን እለት እለት እያሻቀበ የመጣውን የህትመት ዋጋ ለመቋቋም ሲሉ በዚህ አይነት ተጽእኖ ውስጥ መግባታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው:: ነገር ግን አሁን በሀገራችን በህትመት ላይ የሚገኙትን በተለይ ከፋይናንስ ተጸእኖ ውጪ ያሉትንም ፖለቲካዊ ጫናዎች ተቋቁመው በነጻነት ያለ ፍርሀት የጋዜጠኝነት ስራቸውን ለሚሰሩ ምስጋና ቢያንሳቸው እንጂ አይበዛባቸውም:: እኔም ለስራቸው መገን እላለሁ::

ማጠቃለያ

የሀገራችንን የሚዲያ መልእካ፡ምድር በአንድ ተራራ እንመስለውና :ይህንን ተራራ ለሁለት የሚከፍል ትልቅ ሸለቆ አለ ብለን እናስብ :: ከተራራው ግርጌ እስከ ጫፉ ድረስ ያለውን ምቹ እና ገላጣ ስፍራ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን የሚባሉ መጥቀስ ቢያስፈልግ ፦ኢቴቪ፡የኢትዮጵያ ራዲዮ : አዲስ ዘመን : ሂራልድ: FM97.1 አሁን ደግሞ በየክልሉ ያሉ የመንግስት አዳዲስ የክልል ኢቴቪዎች እና የግል ወይም ነጻ የሚል ቦሎ ለጥፈው በልማታዊ ጋዜጠኝነት ስም በመዝናኛ እና ስፖርታዊ አደንዛዥ ወሬዎች አየሩን የተቆጣጠሩ የሰፈሩበት ሲሆን:: ተራራውን ለሁለት በሚከፍው ትልቅ ሸለቆ ውስጥ ደግሞ በመሰናክሎች የተተበተቡ ከህዝብ ጋር ለመገናኝት ወደ ተራራው ገላጣ ስፍራ ለመውጣት ሙከራ ሲያደርጉ በሸለቆው ዳር እና ዳር የቆሙ እና ሰፊውን የተራራ ከፍል የማያስደፍሩ ሰዎች መልሰው ወደ ሸለቆው የሚከቷቸው ራሳቸውን የነጻው ፕሬስ አባላት እያሉ የሚጠሩ በተራራው ገላጣ ስፍራ የሚገኙት ደግሞ የግል ሚዲያ እያሉ የሚጠሯቸው የሚገኙበት የተራራው ክፍል ነው:: በዚህ አይነት ሀገራችን የሚዲያ መልእካ፡ምድር ታዲያ ሊኖር የሚችለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ወይስ የጋዜጠኝነት ጣረ ሞት?

2 thoughts on “በኢትዮጵያ ያለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ወይስ የጋዜጠኝነት ጣረ ሞት?

  1. በማጠቃለያህ ያስቀመጥከውን ይበልጥ ወድጄዋልሁ:: መቼም የመናገር ነጻነት ተነፍጎ ልማታዊ ጋዜጠኝነትን ማስብ ቅዠት ነው:: ለኔ አሁን አገራችን ያለው ፕሮፓጋንዳ ነው:: ልማታዊ ጋዜጠኝነትን ለምከወን ብዙ ብዙ ይቀረናል::

  2. ከአንድ መንገድ አስር ዜናዎች ይፈለፈላሉ የሚለው ከልማታዊ ጋዜጠኝነት ጋር የሚጣረስ አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም ልማታዊ ጋዜጠኝነት ሂደትን እየተከታተለ መዝገብ ግደድ ይለዋል!
    ትንታግ የሚለው ቃል ተገቢ ነውን?

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.